የሐያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ

የሐያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ

የመጽሐፉ ርዕስ :- የሐያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ :  የዘመን ታሪክ ትዝታዬ ካየሁትና ከሰማሁት 1896-1922

ጸሐፊ፦ ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ

የገጽ ብዛት፦ 455

አሳታሚ፦ አዲስ አበባ ዪኒቨርሲቲ ፕሬስ

Description

“በ1909 ዓ.ም ውብ አየሁ እንግዳ የተባለ በአራዳ ጊዮርጊስ የሚቀድስ አንድ ዲያቆን ነበረ። አገሩ በአንኮበር በኩል ነውና ወደዚያ ሄዶ ጥይት አያስነካም የሚባለውን የአቃቤ ርዕስ መድኃኒት አጥንቶ ወደ አዲስ አበባ ተመለሠ። መድኃኒቱ የአስማት ድግምት የሚደገምበት አንድ ዕፅ ነው። ውብ አየሁ በዚያች ዕፅ እየደጋገመ ለየወታደሩ በአምስት፣ በአምስት ብር ይሸጥ ጀመር። ይህንንም ወሬ ደጃዝማች ኃይለ ማርያም ለማ በሰማ ጊዜ ለራሱ ስለፈለገው ውብ አየሁን አስጠርቶ ወደቤቱ ወሰደውና ስለ አቃቤ ርዕሱ ነገር ጠየቀው። ውብ አየሁም ይህን ዓቃቤ ርዕስ ከያዘ ማንም ሠው ጥይት አይነካውም ዋጋውም አምስት ብር ነው ብሎ መለሰለት። ደጃዝማችም “እውነት ከሆነ ዋጋውእንኳ ሲያንሰው ነው” ካለ በኋላ ነገሩን ለማጣራት ሲል፣ “አረ ለመሆኑ ከጥይት ማዳኑን በምን ታስረዳኛለህ” አለው። ውብ አየሁም በአቃቤ ርዕሱ ተማምኖበታልና “በእኔ ይፈትኑብኝ” ብሎ መለሠለት። ከዚህ በኋላ ደጃዝማቹና ውብ አየሁ ከቤት ወጥተው ወደ ሜዳ ሄዱ። ውብ አየሁም አቃቤ ርዕሱን በእጁ ያዘና ጥቂት ራቅ ብሎ በሜዳው ላይ እንደ ዒላማ ቆመ። ደጃዝማቹም ዲሞትፈር ጠመንጃውን አጉርሶ ቃታ ቢስብ በሆድቃው ከተተበትና ውብ አየሁ በግምባሩ ተደፍቶ ወደቀ። ሬሣውም ወደ አራዳ ጊዮርጊስ ተወስዶ ከገረገራ ውጪ ተቀበረ። በዛ ዘመን የውብ አየሁ ነገር በሰፊው ስለተወራ በሁሉም ዘንድ ይልቁንም በቤተክህነት ሰዎች ዘንድ መዘበቻና መተረቻ ሆኖ ከረመ። በውብ አየሁ የደረሰውም ጉዳት በዚህ አይነት ነገር የሚታለል እንዳይኖር ማስጠንቀቂያ ሆነ።” * “አንድ ሰው በሕልሙ ከሌላ ሰው ሚስት ጋር አድሮ ኖሮ «ዛሬ ከእገሌ ሚስት ጋር በሕልሜ አብሬ አደርሁ ብሎ ተናገረ።» የሴቲቱም ባል ወሬውን ሰምቶ «ሚስቴን ደፍሮብኛልና የይናፋ(ይናፋ ማለት የሌላ ሰው ሚስትን በዝሙት የደፈረ ሰው ለባልየው የሚከፍለው የካሣ ገንዘብ ነው) ካሣ ሊከፍለኝ ይገባል» ብሎ ከሰሰው። ነገሩም ከፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ችሎት ደርሶ ይሟገቱ ጀመር። ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ነገሩን ቀበል አድርገው ተከሳሹን «በቅሎ የለህምን» ብለው ቢጠይቁት «አለኝ ጌታዬ» ብሎ መለሰ። እርሳቸውም «እስቲ በቅሎህን ጭነህ ከነሙሉ መሣሪያዋ በቶሎ አምጣ» ብለው አዘዙት። ወደቤቱ ሄዶ በቅሎውን ጭኖ በመጣ ጊዜም «በል ለከሳሽ ስጠው» አሉት። ወደ ከሳሹም ዘወር ብለው «በል እንግዲህ በቅሎውን ተቀብለህ እዚሁ እፊቴ ተቀምጠህበት ሂድ፣ ተደፍረሃል፣ተበድለሃል፣ ካሣህ ነው» አሉትና በበቅሎይቱ ተቀምጦ ደስ ብሎት እያሠገረ ሄደ። ከግቢያቸው ወጥቶ ጥቂት መንገድ ከተጓዘ በኋላ መልእክተኛ ልከው አስጠሩትና ከነበቅሎው ተመለሰ። ከፊታቸውም ሲደርስ «በል እንግዲህ በቅሎውን መልስለት» ብለው አዘዙት። ሰውየውም «ምነዋ ጌታዬ ተፈርዶልኝ የተሰጠኝን ካሣ እንዴት እመልሳለሁ» ብሎ ቢያመለክት፣ «አዬ ጉድ አዬ ጉድ የሁላችሁም ምኞት ነው፣ እርሱ ሚስትህን በሕልሙ አያት እንጂ አላገኛትም፣ አንተም የተመኘኸውን ካሣ ይኸው አይተኸዋልና ይበቃሃል፣ እንግዲህ በየቤታችሁ ግቡ» አሰናበቷቸው፣ ተከሳሹም ከነበቅሎው ወደቤቱ ገባ።….”

Reviews

There are no reviews yet.

Be the first to review “የሐያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ”

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Style switcher RESET
Body styles
Color settings
Link color
Menu color
User color
Background pattern
Background image